top of page

                                         

ኡበር                                                                                                      1                                                                                                                                                                   ​

ኡበር

 

                                               አጭር ልቦለድ

                                                በ የ ባህራን

 

ትራፊኩ ያለወትሮው ይትርመሰመሳል። 'ኡበር' የተሰኘውን ይህን የታክሲ አገልግሎት መስጠት ከጀመርኩ ወዲህ የኦስሎ ጎዳናዎች እንደዚህ ስራ በዝቶባቸው አይቼ አላውቅም። የእግረኛውም ቁጥር ቢሆን የትየለሌ ነው። ሃገርህን ልቀቅ የተባለ ይመስል ካንዱ የመንገድ ዳርቻ ወደሌላኛው የተሰመሩለትን ነጠብጣቦች ተከትሎ ይተማል።

 

"ምን ሊሆን ይችላል" ራሴን ጠየቅኩ። ላፍታ ከፊትለፊቴ ካለው መንገድ አይኔን ነቅዬ ካጠገቤ ወንበር ላይ የተቀመጠውን ሳምሶናይት እየተመለከትኩ። ከሰከንዶች በፊት ነበር አንድ ከትከሻው ሰፋ ሰፋ ያለ ራስ ቅሉ ላይ ያሉና በሽሽት ላይ የሚመስሉ ቅንጥብጣቢ ጠጉሮቹን ወደ ላይ ያጎፈረ ፂሙን እንደ ጳጳስ ያንዠረገገ ወጠምሻ ምንነቱን ያላወቅኩት ሳምሶናይት አስታቅፎኝ እብስ ያለው።

 

እኔ በመሰረቱ ይህንን ስራ ስጀምር ሰው እንጂ ቦርሳ አመላልሳለው ብዬ አልነበረም። ጎረምሳው ባደረገልኝ ጥሪ መሰረት ከአስፋልት ዳር ስጠብቀው ከተፍ አለ። አልዘገየም። 

 

"ሃሎ" አለኝ በጎርናና ድምፁ የመኪናዬን የፊት ለፊት በር ከፍቶ።
"ሃሎ" አልኩ መልሼ። ሃሎ አለማቀፋዊ ቋንቋ ነው ብዬ ስላመንኩና በምንኛ እንደሚያወራኝ እስካውቅ ሌላ ቃል አልተነፈስኩም።

 

አሁን አሁን የኖርዌይ ዋና ከተማ የሆነችው ይቺህ ትንሽ መዲና የዐለም ህዝብ መናሃሪያ ሁናለች እድሜ ለአምባ ገነን መሪዎችና እነሱ ለፈጠሩት ፍልሰት። የኖርዌ ነዳጅ ማፍለቅ እና የሆሊውድ የፊልም ኢንደስትሪም የፈጠሩት መነሳሳት አክብሮት ሳይቸረው የሚታለፍ አይደለም።  

 

ብቻ እዚህች የዐለም ህዝቦች ቋት የሆነች መዲና ውስጥ ያለው ሰው ቋንቋው እንደየ ገጹ ይለያያልና እሱ ፍንጭ እስከሚሰጠኝ ቃል አልተነፈስኩም። 

 

"የሚሄደው ይሄ ነው።" አለ በሁለት እጁ እንደበኩር ልጁ ታቅፎት የነበረውን ጥቁር ሳምሶናይት እንደ እንቁላል ተንከባክቦ ካጠገቤ በሚገኘው ወንበር ላይ እያኖረው። ፍቅረኛውን እንዲህ ሚንከባከብ ከሆነ መቼም አይለያዩም ስል አሰብኩ።ቁጣ አዘል ድምጹ ግን አላስደሰተኝም። "የሚሰበር ነው። ጓደኛዬ በመዳረሻ አድራሻው ትጠብቅሀለች።" የአፍ መፍቻው እንዳልሆነ በሚያሳብቅበት እንግሊዘኛ ቀጠለ። "ለእርሷ ስጥልኝ አደራ!" እኔ ስለ አደራ መብዛት መጥፎነት የሚያወጋ አባባል ለቀልድ ያህል ጣል ለማድረግ ስጣጣር እሱ ከድምጹ በተቃራኒ ቀጭን ትዕዛዙን አስተላልፎ በሩን በላዬ ላይ እንደጠላት ገንዘብ ወርውሮብኝ ሄደ። በውስጤ እያጉረመረምኩ በመስማማት ራሴን ወደ ላይና ወደ ታች ነቀነቅኩ።

 

መዳረሻ አድራሻውን ከፊት ለፊቴ መስታወት ላይ በተለጠፈው ቴሌፎን አረጋገጥኩ። 'አስር ደቂቃ ...' ወጠምሻው ቻው ሳይለኝ ቀልቤን ገፎ በሩን ጠርቅሞብኝ እየተንገዋለለ ከሄደ ወዲህ ይኸው አንድም በሰውየው ምግባረ ጎዶሎነት አዝኜ: አንድም በሳምሶናይቱ ምን ይሆን ጥያቄ ተወጥሬ መሃል ኦስሎ ጎዳና ላይ አለው።

 

                                                                                       

bottom of page