top of page
ኡበር                                                                                                                                                                                                 2
 

"ምን ይሆን? ለምንድነው ሰውየው በጥንቃቄ ያስቀመጠው? ደግሞስ እንዳይሰበር ከፈለገ በጨርቅ ይጠቀልለውም?" በጭንቅላቴ ከሚመላለሱ ጥያቄዎች ጥቂቶቹ ነበሩ።በጥያቄዎቹ ተመስጬ ነው መሰል የጎዳና ላይ ቀይ መብራት አልፌ ልነዳ ለጥቂት ተንሳጥጬ ቆምኩ።  'ሁሁሁ ...' በረጅሙ ተነፈስኩ። ቀዩ መብራት በቸረኝ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ያን ካጠገቤ ተቀምጦ የሚታዘበኝን ነገር ደገምገም አድርጌ በጨረፍታ ተመለከትኩት። 'ቀለም በእይታ የሚለቅ ቢሆን ይህ ቦርሳ ቀለም አልባ ይሆን ነበር' ስል አሰብኩ።

 

"ሰውየው ግን ምን ሁኖ ነው? መልካም መንገድ! ይቅር: ቻው ይቅር እሱማ የፃድቃን ነው ... ምናለ ትዕዛዙን መረዳቴን እንኳ በቅጡ ቢያረጋግጥ:: ምንስ ያሯርጠዋል?" ሰውየውን ከመታዘብ አልፎ ገመትኩት። ትዝብቴ ወደ ጥርጣሬ የተለወጠው ግን በስልኬ ላይ በጉልህ ተቀምጦ ያለውን የስሙን መጠሪያ ስመለከት ነበር 'ኤም አር' ይላል። "ኤም አር ኤም አር ... 'ሚስተር' አቶ መሆኑ ነው" ፈገግ ለማለት ብሞክርም አልተሳካልኝም። ፈገግታዬ እንደ ኖርዌይ በጋ መኖሩን እንኳ ሳላጣጥመው እፍ አለ። ምክንያቴ ደግሞ በኡበር ገጽ ላይ የብዙ ሰዎችን ስም ለማየት በመታደሌና እንደዚህ የማዕረግ ስሙን ብቻ ያስቀመጠ ሰው እሱን ብቻ ማየቴ ነበር።

 

"ምን መደበቅ ፈልጎ ነው? መቼም ስሙ አቶ አይደለም።" ከበስተኋላዬ የቆመች ትንሽ የቤት መኪና ከአቅሟ በላይ ስታንቧርቅ ነበር የጎዳናው መብራት ወደ አረንጓዴ መቀየሩን ያስተዋልኩ። ከመቅጽበት ለማስነሳት ስሞክር የመኪናዬ ሞተር ጠፋ። ተደነባበርኩ። ከበስተኋላዬ የተኮለኮሉ መኪኖች ልክ እንደ አምባገነኖች ፓርላማ የትንሿን መኪና ጩኸት ተቀብለው አስተጋቡ። አካባቢው ታወከ። እኔም አምባረቅኩት ለምን...? አትጠይቁኝ። በድጋሚ በረጅሙ ተንፍሼ ሞተሩን አስነሳው። ከእኔ: ከትንሺቱ መኪና እና ከበስትኋላዋ ካለው የፖሊስ መኪና በቀር ግን መብራቱን ማለፍ የቻለ አልነበረም።

 
bottom of page