ሰላም ምን ያደርጋል?
ሰላም ምን ሊፈይድ ሰላም ምን ያደርጋል?
ወኔን አሽመድምዶ ጡንቻን ያሟሽሻል
ጀግንነትን ሰርቆ በቁም አንበርክኮ በዳዴ ያስኬዳል
ሆ ... በል ያገሬ ሰው ነጋሪት ይነፋ
የሰው ነብስ እንገብር የለማውም ይጥፋ
በውሃ ቀጠነ በቆዳዬ ጠቦኝ ሰበብ እንስራና
እንፎክር... እንጨፍር... እንሂድ ከጎዳና
ዳሩ:
ጎዳናው ማን አለው እኛ ካልጮህንበት
ሰላም ተጋግሮበት ሰላም አይበላበት
ምክንያት?
ምክንያት ምን ሊፈይድ ምክንያት ማንን በጀ?
ማነው የገነነው ማን ታሪክ አወሰው ቀመር ስላበጀ?
ፍቅር...እናት...ሃገር ህሊናን ቆፍረው ከልብ ስር ቀሪ
እነሱን ማውሳት ነው ትውልድ እንዳይረሳን ታሪክ እንዲያወሳን እንዲኖር ቀባሪ
ጥቁር ነህ ነጭ ነህ
ወጣት ነህ አዛውንት ጊዜው የማይገባህ
የተማርክ ያልተማርክ ገበሬ ከተሜ ከሌላው የጸዳህ
ብለን እንከፋፍለው ይሰለፍ ከኛ ዘንድ
እኛን ምን ገደደን ሃገር ቢበጠበጥ ሃገር በሳት ቢነድ
እከሌ ከታች ነው እከሌ ከላይ ነው እከሌ ነገሰ
አነተ ባሪያ እኮ ነህ ጊዜ ያዋረደህ ዋጋህ ውል የሌለው ከጥንብ የረከሰ
ይሄንን አትየው አላፊውን ጊዜ ያንተ ነው ቀጣዩ
'እልፍ ሲሉ እልፍ' ሰጪ ነው የላዩ
ብለን ከነገርነው ብለን ከሰበክነው ማይጓጓ ማን አለ?
ዛሬ እንዳቀረቀርክ ዛሬ እንደሰገድክ ነገ አሰጋጁ 'መሪ' ከተባለ
ስለዚህ ያገር ሰው
ብናጣ ንብረት ነው
ብንገብር ወገን ነው
ሁሉም ይካካሳል ሲመጣ ስልጣኑ
ብቻ እንሰይጥን እኛ ቀርቶ መሰልጠኑ
ብቻ መበርታት ነው ይፋፋም አመጹ
ደም ካላሳየነው አይጠፋም ችግሩ አይጠራም ህጸጹ
ሰላም መነጋገር መወያየት እንደው ድሮም መጤ ቃል ነው
ጥልያን እየዘራ እኛን አዘናግቶ ትሩፋቱን ደግሞ ጥልያኑ ሚያጭደው
የ ባህራን
4 የካቲት 2008
