ይድረስ ለአሞራው፥
ቡርቅቅ ግዛት ይዘህ፥
ማናለብኝ ብለህ፥
ካንዱ ጥግ ወዳንዱ ለምትዛወረው፥
ለሰማዩ ጌታ፥ ይድረስ ለአሞራው።
አታውቀኝ ይሆናል፥ እኔም አላውቅ ህም፥
እኔ ምኖር ተዚህ፥ አንተ ምትኖር የትም።
ይህንን ደብዳቤ ልጥፍ ያነሳሳኝ፥ ዋናው ቁምነገሩ፥
ናፍቀኸኝ አይደለም ወዲህ ነው ነገሩ።
በአዲስ አባ ጠሃይ፥ አዳፋ ቱታዬን እንደተከናነብኩ፥
ከስራ ወደ ቤት እያቀናሁ ነበርኩ።
መቼም ታውቅ ይሆናል፥ የቤቴን ገበና፥
ሚስት ድስት የሌለኝ መናጢ ነኝ ገና።
አንተን ያገኘሁ ለት፥ መሃል ተከተማ፥ እጅግ ስለራበኝ፥
ጥብስም ስለከጀልኩ፥ በቆሎ ሸምቼ፥ ከመዳፌ አኖርኩኝ።
መቼም ጥብስ ስልህ፥ ትሳሳት ይሆናል፥
አንተ ምን አለብህ፥
ዋጋ አይንርብህ፥
ቀረጥ አይጣልብህ፥
ቪዛ አትጠየቅ፥ ድንበር የለሽ ሁነህ፥ አንዴ ተፈጥረሃል።
እና እንደነገርኩህ፥
በቆሎየን ስግጥ ከእጄ አኑሬ፥
ከየት መጣህ ሳልል፥ አያ አሞራ አጅሬ፥
አውቀህ ይሁን ሳታውቅ፥ ማእዴ አናት ላይ፥
መጣል የሌለብህ፥ ምናልባት ጠቃሚ፥ እቃህን ጥለሃል።
ልከስህ አልሻም፥
እዚህ ተከተማ ፥ላንተ ሚመጥን ወህኒ አልተሰራም::
ልጣላህም አደል፥
ከኣቻዎቼ ጋር የተቀያየምኩት፥ ያላወራረድኩት፥ የጠብ ደብተር ስላል።
ካሳም እልፈልግም፥ ያንተን ችሮታ፥
ጦሜን እንደው አደርኩ፥ ርቄ ከገበታ።
እኔ ምከትበው፥ ይህቺን ቅንጣት ክታብ፥
ልጅ መሆኑን ትተህ፥ ልብ ገዝተህ አደብ፥
ምትመልስልኝ፥ ጥያቄ ይዤ ነው፥
እነሆ ጥያቀው፥
“ተላ……….ይ፥
ተሰማይ ላይ፥
ታለህበት ስፍራ፥
ወደታ……ች ስታይ፥ ተኛ ተድሆቹ፥ ከምስኪኖች ተራ፥
`የሰው ልጅ` ነው ምታይ ወይስ `ቆሼ ተራ`”?
ከ እኔ፦
`የ ባህራን
