top of page

ገዳይ መሆን ይበጃል

 

ክስተት አንድ:-

ሃገሬው ከተስማማበት ከጻፈው ህግጋት መሃል

በማወቅ ያጎደለለት በንጉስ ዘቦች ተይዧል

ተቃውሞ አንድ:-

«እኚህ ንጉስ ተብዬ ከነ ሹማምንታቸው

በያዙት ምስኪን ፍጡር ላይ እንዲሞት መወሰናቸው

አግባብም ደግም አይደለመጽሃፍ መች ፍረድ አለ»

መንደሩ አጨበጨበ ባዋቂው እየተመራ

ንጉሱን ከቶ አወገዘ ቁጠው ገንፍሎ ኑሮ ነፍጥ ምንዥር መዘዘ

ከቤተ መንግስት ተሞም ሌላ እንዲሾም አዘዘ

ተቃውሞ ሁለት:-

«አንዱን ባንዱ ብንተካ ከድጥ ወደ ማጥ ሆነ

ፊተኛው ለያዘው ሰይጣን ኇለኛው ፈጽሞ አዘነ

ሞቱን ባንቀበለው ይለቀቅ ብሎ ለመነ

አምላክስ ቢሆን ሩህሩሁ ሳጥናኤል መች ይማር አለ

ሰይፍና እሳት አዞለት ዶለው ከብረት ምጣድ በፍም ነበልባል ከጋለ»

ሌላ ጭብጨባም ህነ ባሳቡ ሁሉ ተስማማ

ሌላ ወራሽም ተተካ ፊተኛው ዙፋን ተቀማ

ተቃውሞ ሶስት:-

«ካላችሁ ደፋር ይሄ ነው መፍረድን ለናንተ ብሎ

ስልጣኑን ለኛ የቸረ ካባውን ለግሉ ቸሮ

እኔ እስከሚገባኝ ፌዝ ነው ፍረዱ ማለት

እንዲፈርድ አኖርነው እንጂ ዙፋኑ ማንን ቆርቁሮት»

ሃገሬው ደግሞ ዶለተ አመጸ በገዢውም ላይ

ተተኪ ንጉስም ጠፋ የሚዳኝ ይህንን ጉዳይ

ክስተት ሁለት:-

«በጅራፍ ይታለፍ» ያለው በይማር ዜማ ተዋጠ

«ይገደል» የሚል ፉከራ ተሰማ ጩሀት ቀለጠ

ባገር የሚዳኝ ጨፍቶ ያንዱ አንዱን መንቀፍ አንጀት አላርስ ብሎ

ነፍጥም ይማዘዝ ገባ በቃል መግባባት ከብዶ ያገሬው ንዴት ንሮ

ክስተት ሶስት:-

ከዚያች ትንሽ መንደር ውስጥ ሁከት ከነገሰባት አንድ ሰው ብቻ ተረፈ

ከንፈሩን እየመጠጠም እንዲህ ተናግሮ አለፈ

«ተቃውሞን ሙያው ባረገ ያውቃለው ትውልድ መሃል

ዳኛ ከመሆን ይልቅ ገዳይ መሆን ይበጃል»

 

ታደለ ወርቁ (የ ባሕራን)ጥር 23, 2008

bottom of page