top of page
የደመራ ፍርድ
 
ኑሮ ዐቀበት ሁኖባቸው መፈጠራቸውን የጠሉ፥
ሁለት አዳፋ ለባሽ ባልንጀራዎች ነበሩ።
አንዱ ለነብሱ ያደረ ባልንጀራውን አፍቃሪ፥
ሌላኛው ደግሞ እጅ ነካሽ ለሆዱ ብቻ አዳሪ።
 
ታዲያ አጋሰሱ ሰው ከዕለታቱ በአንዱ፥
በቀኙ ተነሳ መሰል ለሱ ነበረች ዕድሊቱ።
ከፈረንካው ላይ ቀናንሶ በገዛት ብጣሽ ሎተሪ፥
ንዋይ መጣለትና ሆነ ብስራት ነጋሪ።
ምሽቱ አልነጋ ብሎት በሃሴት መንፈስ ሰከረ፥
ጨፈረ ጨፈረ ጨፈረ …
ድህነት አድዮስ ብሎ ላንቃው እስኪሰነጠቅ ጮ … ክ ብሎ ዘመረ፥
ዐቅሉን ስቶ ተደሰተ ዙርያ ገቡንም አበሰረ፥
ከተዘነጉት መሃል ግን … ውሃ አጠጩ ሰው ነበረ።
 
ሲያገኝውም እንዲህ አለው፡-
«ድህነት ከንግዲህ አበቃ ድሃም አይመጥነኝም፥
ወዳጅነታችንም ይቋጭ ከንግዲህ ላይህ አልሻም።»
በዚህም ድርጊቱን ሳይቋጭ:-አዳፋ ልብሱን አውልቆ ከደመራው ላይ ሞጀረ፥
የድህነትና ድሆችን ከዙርያው መራቅ ዘከረ።
 
ይህ ምስኪን:-
ኪሱን በወደዱለት አዲስ ጏደኞች ተከቦ የመሰቀል ችቦን ሲሞቅ፥
በሳት እንዲለበለብ ከወረወረው አልባስ ውስጠ ሎተሪው መኖሩን አያውቅ!
 
መነሻ ታሪክ የህዝብ
 
ታደለ ወርቁ (የ ባህራን)
28.01.16 EC
bottom of page