top of page
 
 

አሁን ነው ማወቄ

 

ቁሩ ሲበረታ
ምድሩ በበረዶ ማለፊያ ሲነጣ
ሰዉ ተመጣፊያ መጣፊያ ደርቦ ተጨማምቶም እንኳ ቆዳው ገረባብጦ ፊቱ ቢገረጣ
እኔ ግን አለሁኝ
እኔ ግን ነደድሁኝ
እልፍ አእላፍ ተጉዞ ወደኔ የመጣ ጠሀይ እየሞቅሁኝ
የአስራ ሶስት ወር ጸጋሽ በረከትሽ ደርሶኝ
ብቸኝነት ነግሶ ካለሁበት ቀዬ
ያላንዳች አጃግሬ ብቻዬን ቁጭ ብዬ
ድምጽ ከሌለበት
ዝር የሚል ወፍ እንኳ ታሪክ ከሆነበት
ከዚያ ከመንደር ውስጥ ልጄ ሆይ እያለ ዜማሽ ይሰማኛል
ትዝታሽ ወሮኛል
ያንባሰል የባቲ ጨዋታሽ ደርሶኛል
ያ መልካም ጠረንሽ ከሩቅ የሚጣራ 
ደርሶኛል እማማ ወንዙን አቆራርጦ ተሻግሮ ተራራ
የምድር ምህዋር ዐይኔ ሚያካልለው ምን እንኳ ቢሞላ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም እንጂ መች አይቶልኝ ሌላ
ተመራምሪያለው ብዙ ተጠብቤ 
ብዙ ተጨንቄ
በሌለሽበትም የመኖርሽ ምስጢር ቅኔን የተረዳው አሁን ነው ማወቄ
ለካ ጠረን ድምጥሽ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም መልክሽ
ስላለም አይደለ ተዚህ ተከተማ
ጠረንሽ ሚደርሰኝ ድምጥሽን ምሰማ
ነገሩ ወዲህ ነው
የእናትነት ፍቅርሽ እንዲህ ተሰንቅሮ ዘሩን የሚዘራ
ለካስ ከውጭ አደል
ለካስ ከልቤ ነው
ማደሪያ የሰራ

 

የ ባህራን

1 ታህሳስ 2007

bottom of page