የቫላንታይን ወይም የቅዱስ ቫላንታይን ቀን
እ.ኤ.አ ፌብሪዋሪ 14 በሃበሻ የካቲት 6 የሚከበረው: የቫላንታይን ወይም የቅዱስ ቫላንታይን ቀን በመባል የሚታወቀው በተለይ በካናዳ እና በዩ.ኤስ.ኤ. በሰፊው የሚከበረው የቅዱስ ቫላንታይን ክብረ በዐል አጀማመር ብዙ አመታትን የኋልዮሽ ይጓዛል። ይህ የትም ሃገር ቢሆን በህዝባዊ ክብረ በዐልነት ያልተመዘገበ በአሁኑ ሰዐት በመላው ዐለም ተቀባይነት ያገኘ ዕለት መነሻ የሚያደርገው በጥንታዊ ሮም ስልጣኔ በነበረ ሰማዕት ሰው ዙርያ በሚነገር አፈ ታሪክ ነው። ሰውየው ስሙ ቫለንቲን ይባላል። ይህ የሮማው ቅዱስ: ቄስ ሲሆን ሰማዕት የሆነው በ269 ምዕተ ዐመት ከክርስቶስ መወለድ በኋላ እንደሆነ ይነገራል። በቅዱሳን መዝገብ የሰፈረው ደግሞ በ496 ምዕተ ዐመት ከክርስቶስ መወለድ በኋላ በወቅቱ የሮም ሊቀ ጳጳስ ጋሌስዩስ ነበር።
ገድሉም እንዲህ የላል:
ቅዱስ ቫላንታይን ክርስትና እምነቱን እንዲቀይርና ጣኦት እንዲያመልክ የቀረበለትን ጥያቄ እምቢ በማለት ለእስር የተዳረገ በአሳሪው የወቅቱ የሮም ንጉስ ክላውዲዮስ ሁለተኛ ስቃይ ቢደርስበትም የአሳሪውን ልጅ ጁሊያ ከዐይነስውርነት በማዳን ደግነትን ፍቅርን ያስተማረ ሰማዕት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም "ያንቺው ቫላንታይን" የሚል ካርድ በመጻፍ ለጁሊያ የላከው ራሱ ቫላንታይን ከመሰቀሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ እንደነበር ይነገራል። ይህ "ያንቺው ቫላንታይን" አገላለጽም በዘመናዊ ደብዳቤዎች ላይ በሰፊው በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። ጁሊያም ቫላንታይን ተቀበረ ተብሎ በሚገመትበት በሮም አጠገብ በሚገኝ የቅዱስ ሂፖሊቱስ የመቃብር ስፍራ ሮዝ ቀለም ያለው ዛፍ የተከለች ሲሆን ዛፉ የፍቅር እና የጓደኝነት ተምሳሌት ተደርጎ ይወሳል።
በሌላ አፈ ታሪክ ደግሞ ቅዱሱ ቫላንታይን በወቅቱ ጋብቻ እንዳይፈጽሙ በሮም የተከለከሉትን የሮም ወታደሮች በቤተክርስቲያን ደንብ ይድር እንደነበር ይናገራል። ያገቡ ወንዶች ለውትድርናው እንደማይጠቅሙት የተገነዘበው የወቅቱ ንጉስ ክላውዲዮስ ሁለተኛም አንዱ ቅያሜ ከዚህ እንደሚጀምርም ይወሳል። ቅዱስ ቫላንታይን ወታደሮቹ የእግዚያብሄርን ፍቅር እና መሃላቸውን እንዳይዘነጉ በልብ ቅርጽ ብራና እየቀረጸ ይሰጥ እንደነበር ታሪክ የሚነግረን ሲሆን ዛሬ ዕለቱ ሲከበር የልብ ቅርጽ በብዛት ከጥቅም መዋሉ ከዚህ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ ይነገራል።
እውነታዎች፥
- ከስሙና በየካቲት 14 በቪያ ፍላሚኒያ (ከሮም ወደ አፔኒነ ተራሮች የሚወስድ ጥንታዊ ጎዳና) ኢታሊያ ከመቀበሩ በቀር ምንም ስለሱ የሚታወቅ ነገር የለም በሚል በ1969 የ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ከቅዱሳን በዐላት መዝገብ ሰረዘችው።
- የቅዱስ ቫላንታይን ክብረ በዐል የጾታዊ ፍቅር ታሪክ ቅርጽና ይዘት የያዘው ጂኦፈሪ ቻውሰር የተባለ እንግሊዛዊ ሃያሲ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ስለ ቫላንታይን ከጻፈው ግጥም ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይገመታል።
የመረጃ ምንጮች
https://en.wikipedia.org/wiki/Valentine%27s_Day
http://www.gotmedieval.com/2009/02/happy-valentines-from-geoffrey-chaucer.html
